በጎንደር ከተማና አካባቢ በሚገኙ የባህል ሃኪሞች ባህላዊ የዕፅዋት መድሃኒት ቅመማ፣ አዘገጃጀት፣ በሽታ የመለያ ዘዴና አሰጣጥ ትንተና

Authors

  • ሐብታሙ አቃናው

Keywords:

-የዕፅዋት መድሃኒት, ቁሳዊ ባህሎች, ትዕምርታዊነት, ምስጢራዊነት, የዕፅ ማንገሻ ጸሎት, ሃገረሰባዊ ክዋኔ, የቀንድ ካራና የወይራ አንካሴ

Abstract

ባህላዊ ህክምና በስሩ በርካታ የባህል መድሃኒት ዘርፎችን ያቅፋል፡፡ በተለይ ከባህላዊ መድሃኒት ዘርፍ ውስጥ የዚህ ጥናት ትኩረት የሆነው ባህላዊ የዕፅዋት መድሃኒት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ባህላዊ መድሃኒት ከጥንት ጀምሮ ዛሬም ድረስ በተለያዩ ማህበረሰቦች ዘንድ በህክምናው መስክ ከፍተኛ የሆነ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሀገረሰባዊ የዕውቀት ዘርፍ ነው። ጎንደር ከተማም ቀደም ባሉት ዘመናት የስልጣኔ፣ የፖለቲካ፣ የንግድ፣ የሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች መነኻሪያ እና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና በመገኘቷ ምክንያት የባህላዊ መድሃኒት ዕውቀቱ ያላቸው ሰዎች በቤተክርስቲያን በኩል ለተለያዩ ትምህርታዊ ተግባራት ወደ ከተማዋ በመግባታቸው የባህላዊ መድሃኒት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። የዚህ ጥናት ዋና ዓላማም “በጎንደር ከተማና አካባቢ በሚገኙ የባህል ሃኪሞች ባህላዊ የዕፅዋት መድሃኒት ቅመማ፤ አዘገጃጀት በሽታ የመለያ ዘዴና አሰጣጥን” አጠቃላይ ሁኔታ መመርመር ነበር፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በዒላማዊ የንሞና ዘዴ የተመረጡ በጎንደር ከተማና አካባቢ የሚኖሩ ስምንት ባህላዊ የዕፅዋት መድሃኒት አዋቂዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የባህል መድሃኒት አዋቂዎች በዒላማዊ የንሞና ዘዴ የተመረጡትም ስለ ባህላዊ መድሃኒት ከፍ ያለ ዕውቀትና የተሻለ መረጃ ያላቸው በመሆናቸው ነው፡፡ ከእነዚህ የጥናቱ ተሳታፊዎች መረጃ የተሰበሰበው ደግሞ በተሳትፏዊና ጽሞናዊ ምልከታዎች እና በቃለመጠይቅ ነው፡፡ ጥናቱ በተግባራዊ የትውር ንድፈ ሃሳብ ላይ በመመርኮዝ በዓይነታዊ የምርምር ዘዴ የቀረበ ነው፡፡ የተገኙት መረጃዎችም በይዘትና ገላጭ የመረጃ የመተንተኛ ዘዴዎች ተተንትነዋል፡፡ በጥናቱ ሂደት ባህላዊ ሃኪሞች ከተለያዩ የዕፅዋት ዓይነቶች ባህላዊ መድሃኒት ለማዘጋጀትና ተገቢውን የባህል መድሃኒት ለህሙማን ለመስጠት የበሽታውን ዓይነት ባህላዊ በሆነ መንገድ እንደሚለዩ ለማረጋገጥ ተችሏል። የበሽታውን ዓይነት ከለዩ በኋላም የመድሃኒት ዕፅዋቱን ለመሰብሰብ አንድም ከዕፅዋቱ ተፈጥሯዊ አካባቢ፣ አንድም ከመኖሪያ አካባቢያቸው ካላመዷቸው ዕጽዋቶች፣ አንድም ዕፅዋቱን በመግዛትና ከሌላ ባህላዊ ሃኪም ጋር በመለዋወጥ የሚያገኟቸውን የመድሃኒት ዕፅዋቶች ይጠቀማሉ፡፡ ዕፅዋቱን በመሰብሰብ ሂደትም ለባህላዊ ዕፅዋት መቁረጫ፣ ስር መቆፈሪያና ማዘጋጃ (መቀመሚያ) የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ ቁሳዊ ባህሎችና ዕፅዋቱ ለተገቢው ዓላማ እንዲሰምር ሲባል የሚደረግ የዕፅ ማንገሻ ጸሎት አላቸው፡፡ በተጨማሪም የባህላዊ መድሃኒት ዕፅዋቱን ከመገኛ ቦታቸው ለመሰብሰብና የመድሃኒቶቹን ፈዋሽነት ለማጠናከር የሚያገለግሉ የተለያዩ ልማዳዊ ድርጊቶች ወይም ሃገረሰባዊ ክዋኔዎች ይከወናሉ፡፡ በዚህ ጥናት የተካተቱ የመረጃ አቀባዮች ዕምቅ የሆነ የባህላዊ ዕፅዋት መድሃኒት ዕውቀት ባለቤቶች ሲሆኑ፣ ባህላዊ የዕፅዋት መድሃኒቱን ዘመናዊ በሆነ መንገድ የሚሰራበት ሁኔታ በሚመለከተው አካል ቢታሰብበት አሁን በህክምናው መስክ ያለውን ዕድገት ወደ በለጠ ደረጃ ሊያሻሽለው የሚችል መሆኑን እና የዕፅዋት መድሃኒቱንም ከመጥፋት መታደግ እንደሚገባ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

Downloads

Published

2020-12-09